የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች በአፋር እና አማራ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች እና አካባቢዎች ጎብኙ


8/23/2021 8:23:40 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች በሦስት ቡድን በመከፈል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሕወሃት በፈጸመው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እና በአካባቢው ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ለመጎብኘት ያደረጉትን ጉዞ አጠቃለው እየተመለሱ ነው። በአፋር እና በደሴ በኩል ጉብኝት ያደረጉት አመራሮች ጉብኝታችን ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ሲሆን በጎንደር በኩል ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የአመራር ቡድን ነገ ማክሰኞ ነሐሴ 18 ጉብኝቱን አጠናቆ እንደሚመለስ ታውቋል። በአፋር ክልል በኩል ጉብኝት ያደረጉት አመራሮች ሰመራ ከተማ በመገኘት ከክልሉ አደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ከክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር በክልሉ ያሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ወደጭፍራ በማምራት ሕወሃት በፈፀመው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የሚገኙበትን ሁለት ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያዎችን ጎብኝተው ያለውን ሁኔታ ለመረዳት ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በጭፍራ ከሚገኙ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል። በጭፍራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በጭፍራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች የክልሉ አደጋ ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም እና የቀይ መስቀል ማኅበር በኩል እገዛ እያገኙ ቢሆንም ተጨማሪ የምግብ እና የሕክምና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ለመረዳት ተችሏል። በደሴ በኩል የተጓዙት አመራሮች ሕወሃት ጥቃት ከፈፀመባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ በሚገኙ አምስት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የጎበኙ ሲሆን በግዳጅ ላይ እያሉ አደጋ ደርሶባቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላትን አግኝተው አበረታተዋል። ሕወሃት ባደረሰው ጥቃት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የሚገኙ ዜጎች ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች የሚደንቅ ድጋፍ እያገኙ የሚገኙ ሲሆን የከተማው ነዋሪ በራሱ ተነሳሽነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተደራጀ መልኩ የሚፈፀም እንዲሆን ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደሚገባ በቦታው የተገኙት አመራሮች ተረድተዋል። መንግሥት እና ግብረሰናይ ድርጅቶችም በመጠለያ የሚገኙ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን እገዛ ለማድረስ በበለጠ ፍጥነት መሥራት እንደሚገባቸው ታዝበዋል። በጎንደር በኩል የተጓዙት አመራሮች በደብረ ታቦር፣ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞች በመገኘት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እና በግዳጅ ላይ እያሉ ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ የሚገኙ ወገኖችን የጎበኙ ሲሆን እንዚህን ወገኖች ለማገዝ የሚሠራው ሥራ የተቀላጠፈ እና የተቀናጀ መሆን እንደሚገባው ታዝበዋል። አመራሮቹ በየአካባቢው ያሉ የኢዜማ አባላት በቀበሌ እና በወረዳ ደረጃ ሕዝብን ለማንቃት፣ አካባቢው ተደራጅቶ እንዲጠብቅ እንዲሁም የደጀንነት ሥራዎችን ከመንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት በመሆን እያደረጉ ያሉትን ተሳትፎ አበረታተዋል። በጎንደር በኩል የተጓዙት አመራሮች በነገው እለት ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ። ኢዜማ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ እና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚሆን ብር 250,000.00 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል ለመስጠት ቃል መግባቱ ይታወሳል። በሦስት አቅጣጫ ወደሰሜን የሀገራችን ክፍሎች የተንቀሳቀሱት አመራሮች የሚያቀርቧቸው ዘገባዎችን መሰረት በማድረግ ኢዜማ ወደፊት ዝርዝር መግለጫ የሚሰጥ ይሆናል።