የሐዘን መግለጫ


8/26/2021 2:39:18 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

የሐዘን መግለጫ! በምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ማንነት እና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ የማይተካ ሕይወታቸውን ላጡ እና ከሚኖሩበት አካባቢ በግፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን። ምንጊዜም ቢሆን የዜጎችን ደኅንነት (ሕይወት) ማስጠበቅ የመንግሥት ዋነኛ ተግባር በተለይም ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀምባቸው የነበሩና ጥቃት ሊደርስባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን በትኩረት እንዲመለከታቸው እናሳስባለን። ከዚህ በፊት በመግለጫችን እንዳሳሰብነው በፌደራል እና በክልል የፀጥታ መዋቅር እጥረት ምክንያት ክፍተት የሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ላይ ዜጎች እንዲደራጁና ራሳቸውንም ሆነ አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ የማስቻል ሥራ እንዲሠራና በአካባቢው ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች እንዲፈተሹ፤ እንዲሁም ለተፈናቃይዮች እና ቤትና ንብረት ለወደመባቸው አስቸኳይ የሆነ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው መንግሥትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። ኢዜማ በወለጋ ኪራሙ ወረዳ እና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በየዕለቱ እንደቅጠል የሚረግፉ ንፁሃን ወገኖቻችን እንዲሁም ሀገራችን እያሳለፈችው ለምትገኘው ዘርፈ ብዙ ችግር የተሰማውን ከባድ ሐዘን እየገለፀ ፤ ከምንጊዜም በላይ ሁላችንም በአንድነት ቆመን እንደሀገርና ሕዝብ የመጣብንን አደጋ እንመክት ሲል ጥሪውን ያስተላልፋል። የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት!