ዋና ገጽ
አወቃቀራችን
ከፍተኛ አመራሮች
ኢዜማን ለምን ይመርጣሉ?
ዐቢይ መልዕክቶች
ስራ አስፈጻሚ
ዕጩዎች
ትኩረት የተነፈገው በምስራቅ ወለጋ እና አካባቢው በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት በአስቸኳይ ማስቆም ያሻል
10/12/2021 1:08:56 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ
ትኩረት የተነፈገው በምስራቅ ወለጋ እና አካባቢው በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት በአስቸኳይ ማስቆም ያሻል በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ እና ሆሮ ወረዳ - ሎሚጫ፣ ተሉሞቲ፣ ቦቶሮ፣ ቦራ፣ ወለጌ፣ ትጌ፣ ኮትቻ፣ ጋሬሮ፣ ጎርቴ፣ አርቡ ሲንታ፣ አርቡ ሶቴ፣ ገበርጉን 2ኛ፣ ኢዶ ቦቲ እና ሌሎች አከባቢዎች የሚኖሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ ማንነታቸውን መሰረት አድርጎ እየተፈፀመ የሚገኘው አሰቃቂ ጥቃት ጊዜ እየጠበቀ እያገረሸ አሁንም የወገኖቻችንን ውድ ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ንፁሃን ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከመጠቃታቸው በፊት ስጋታቸውን በአካባቢያቸው ላሉ የመንግሥት አካላት ሲገልፁ ቢቆዩም የዞኑ አስተዳደር አባላት «በቁጥጥራችን ስር ነው/የሚያሰጋ ነገር የለም» እያሉ ብዙ ወገኖችን አጥተናል። መንግሥት በአካባቢው ያለውን የአስተዳደር መዋቅር እንዲፈትሽ በተደጋጋሚ ያሳሰብን ቢሆንም ይህ ነው የሚባል እርምጃ ባለመወሰዱ ጥቃቶቹ አሁንም ቀጥለዋል። አካባቢው ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር መገናኛ መንገዶቹ ተቆፋፍረው በታጣቂዎች በመዘጋታቸው ምክንያት እንቅስቃሴ ተቋርጦ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ህክምና፣ መድኃኒት፣ ሸቀጣሸቀጥ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ከሆነባቸው ሰነባብቷል፤ የመሳሪያ ድምፅ እየሰሙ የሚውሉ ህፃናት እጅግ ተሸብረዋል። ንፁሃንን ለመታደግ በቦታው ያሉ የፌደራል የፀጥታ አካላት ቁጥራቸው ጥቂት በመሆኑ ሕዝቡን መታደግ ካለመቻላቸው ባለፈ እነሱም የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ ኢዜማ ከቦታው በደረሰው መረጃ አረጋግጧል። የጥቃቱ መደጋገም እና ተመሳሳይነት የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን የሚገባው መንግሥት ለጉዳዩ የሚገባውን ያክል ትኩረት እንዳልሰጠው አመላካች ሆኖ አግኝተነዋል። በተደጋጋሚ የሚደርሱትን ጥቃቶች ለማስቆም እና አጥፊዎችን ሕግ ፊት አቅርቦ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ለምን እንዳልተቻለ የክልሉ መንግሥት እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጡበት እየጠየቅን ከዚህ በፊት በአካባቢው ነዋሪዎች የደረሱ ከሰብዓዊነት ፍፁም የራቁ ግፎች አሁንም በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ዜጎች ላይ ዳግም ሳይከሰቱ እርምጃ እንዲወሰድ እና ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ከሚደርስባቸው የደህንነት ስጋት ወጥተው ሰላማዊ የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ዘላቂ መፍትሄ በአስቸኳይ መሰጠት እንዳለበት ኢዜማ ያሳስባል። የሚወሰዱት እርምጃዎችን በተመለከተም ግልፅ እና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ እንጠይቃለን። የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት