ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርቡ በምክር ቤቱ የኢዜማ አባላት ጥያቄ ቀረበ


10/25/2021 10:52:59 PM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው በሕዝብ የተመረጡት የፓርላማ አባላት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ በመገኘት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ከሚገኘው የህልውና ጦርነት ጋር በተያያዘ ያሏቸውን ጥያቄዎች እንዲመልሱ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ጥያቄ አቅርበዋል። ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም አራቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተወካያቸው አማካይነት ፈርመው ያስገቡት ደብዳቤ የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በይዞታው ሥር ከነበሩ ቦታዎች ለቆ እንዲወጣ መንግሥት ሲወስን በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ከግጭት እረፍት እንዲያገኙ በማሰብ እንደነበር አስታውሶ ግጭቱ ግን ከመቀነስ ይልቅ እንደውም አዳዲስ አካባቢዎችን ወደግጭቱ ቀጠናነት እየጨመረ መምጣቱን እና በቅርቡም የደቡብ ወሎ አካባቢዎችን ስጋት ውስጥ እንደከተተ ይገልፃል። ይህንን መሠረት በማድረግ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መንግሥት በምን ያህል ጊዜ ግጭቱን ቋጭቶ ዜጎች ወደመደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ፣ ዕቅዱን ለማሳካት ከማኅበረሰቡ እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቀው ምን እንደሆነ፣ ከመረጃ ፍሰት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ክፍተት ለማረም እየተሠራ ያለ ሥራ ካለ እንዲሁም አሁን የገባንበት ዓይነት ችግር ውስጥ ተመልሰን እንደማንገባ የሚያረጋግጥ ሥራ እየተሠራ ከሆነ ለምክርቤቱ አባላት እንዲያብራሩ ነው የጠየቁት። የኢዜማ ተወካዮች ጥያቄያቸውን በምክር ቤቱ የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 መሰረት በጽሑፍ ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።