ዋና ገጽ
አወቃቀራችን
ከፍተኛ አመራሮች
ኢዜማን ለምን ይመርጣሉ?
ዐቢይ መልዕክቶች
ስራ አስፈጻሚ
ዕጩዎች
ለትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ፖርቲ እንገነባለን
1/3/2022 2:07:10 PM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ
ለትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ፖርቲ እንገነባለን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በአጭር ጊዜ ከፍፃሜ የሚደርስ የመቶ ሜትር ሩጫ ሳይሆን ትዕግስትን የሚፈታተን የማራቶን ሩጫን ይመስላል፡፡ በየትኛውም ሀገር ያለመስዋዕትነት እና ያለ ትግል ዴሞክራሲ ተወልዶ አያውቅም፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማምጣት እልህ አስጨራሽ ትግሎች ተደርገዋል፡፡ ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ የተለያዩ ዕድሎች የነበሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክኒያቶች ከሽፈው በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ዘመናትን አሳልፈናል፡፡ እስከዛሬ ድረስ እንደ ሀገር ያገኘናቸውን ዕድሎች ያመከንናቸው በመሪዎች ወይም በገዢ ፓርቲዎች ድክመትና ጥፋት ብቻ ነው ብንል ራሳችንን ከኃላፊነት ለማዳን እጃችንን ከመታጠብ ባለፈ እውነታውን ሙሉ በሙሉ የሚያሳይ አይሆንም፡፡ በየጊዜው የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድም በመንግሥት ጫና ሁለትም በውስጣቸው በነበረ ድክመት የመንግሥት ሥልጣንን የያዘውን አካል ለመገዳደር አለመቻላቸው በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ለመኖራችን የበኩሉን ጉልህ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ አማራጭ በሌለ ጊዜ ሁሉ ስርዓቶች ተኪ እንደሌላቸው እና ያለ እነሱ ሀገር የማትቆም እስኪመስላቸው ድረስ እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም የፖለቲካ ባህላችንን ለሀገራችን ህዝብ የዲሞክራሲ ጥማት እና ፍላጎት ተገቢ መልስ የሚሰጥ ሆኖ ማደራጀት እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መንግስት የሚሰራውን ከመተቸት በተጨማሪ በሰፊው አማራጭ ያሉትን ሀሳብ ማቅረብ ሳይችሉ የቆዩበት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም የአቅም ማነስ እና በዚህም ምክኒያት አማራጭ ሀሳብ ለማመንጨት የሚችሉ በቂ ሰዎችን አለመያዝ አንዱ እና ዋነኛው መሆኑ ከኋላ ታሪካችን በቀላሉ ልንረዳው የምንችለው ሀቅ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ መንግሥት ሲሆን ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ወሳኝ ሥራዎች ለመስራት አስቀድሞ ራሱን በመንግሥት ጫማ ውስጥ በማስቀመጥ እና በመንግሥታዊ ቁመና እና ቅርፅ ራሱን ማደራጀት መቻሉ ትልቅ ሚናን ሊጫወትለት እንደሚችል ከሌሎች ሀገር ልምዶች ማየት ይቻላል፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባትን እንደ ትልቅና ወሳኝ ቁምነገር ለሚወስድ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና አማራጭ ሀሳቦች ማሰብ እንደማይቻል ለሚገነዘብ እንደ ኢዜማ ላለ ፓርቲ የመንግሥት ሥልጣንን ቢይዝ ያሉትን አማራጭ ሀሳቦች ለሕዝብ የሚያሳይበት አደረጃጀት እና መዋቅር መፍጠር መቻል በቀጣይ ምርጫ ከሀቀኛ ተፎካካሪ እንዲቆጠር ከማድረግም ባለፈ የሠለጠነ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካን ለሀገራችን የማስተዋወቅና ለማጎልበት ከፍተኛ በጎ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እነሱ የመንግሥት ሥልጣን ቢይዙ ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ እና መንግሥት ባዋቀራቸው የአስፈፃሚዎች (በዋናነት ሚኒስትሮች) ምትክ ማንን ያደርጉ እንደነበር የሚያሳዩባቸው መንገዶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መንገዶች አንዱ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ (shadow cabinet) ማቋቋም ነው፡፡ መደበኛ የትይዩ ካቢኔ የተመሰረተው በእንግሊዝ ሀገር በ 1960ዎቹ እ.ኤ.አ ሲሆን የተለያዩ ሀገራትም ጥቅም ላይ አውለውታል፡፡ ከሀገራችን ወቅታዊ እና ሕጋዊ ሁኔታ አንጻርም የተፎካካሪ ፓርቲነት መዋቅር፣ ልምድ፣ ሰነዶችና መሰል የካበቱ አሠራሮች ባለመኖራቸው ፓርቲዎች ቁመናቸውን በዚህ ልክ ከፍ ማድረግ የሚችሉበት ዕድል ባለመኖሩ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ ሳይሞከር ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአመዛኙ ምርጫ ሲቃረብ ካልሆነ በቀር ገንቢ ሚናቸውን ማሳየት ሳይችሉ፤ አማራጭ ሀሳቦቻቸውን ለሕዝብ በቋሚነት ሳያደርሱ እንዲሁም ራሳቸውን በእውቀትና በመንግስትነት ልምድ ሳያሳድጉ በመጨረሻው የምርጫ ዓመት ብቻ አቧራቸውን አራግፈው ከመንቀሳቀስ በቀር ቀጣይነት ያለው ሥራ ሳይሠሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ምክኒያት የፉክክር ፖለቲካ በሀገራችን ስር ሳይሰድ ጭንጫ ላይ እንደበቀለ ተክል የመጣው ንፋስ ሁሉ ሲወስደው ቆይቷል፡፡ ፓርቲዎች ራሳቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማኖር እና በማንኛውም ወቅት ከአንድ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚጠበቀውን አማራጭ ሀሳብ የማፍለቅ ሥራ ለመሥራት አማራጭ መዋቅራዊ መንገዶችን ማሰስ እና መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የሀገራችንን የዲሞክራሲ ባህል ለማጎልበት የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን በምርጫ 2013ም በነበረው ጉልህ ተሳትፎ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅፍ ይረዳሉ ያላቸውን የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮችን ለህዝብ አቅርቦ ተወዳድሯል፡፡ በተጨማሪም ኢዜማ ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ ከሕገ ደንቡ የሚቀዱ የዲሞክራሲ ስርዓትን ለማሻሻል የሚረዱ ፕሮግራሞችን ቀርፆ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በኢዜማ ሕገ ደንብ የመሪው መዋቅር የትይዩ ካቢኔ እንደሚያዋቅር ይደነግጋል፡፡ የሕገ ደንቡ አንቀጽ 7.1.9 ፓርቲው ስልጣን ላይ ካልወጣ መሪው፣ ዋና ወይም ዋና ያልሆነ የፓርላማ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ከስልጣኑ ጋር ተያይዞ የትይዩ ካቢኔ አባላቱንና ሌሎችንም የትይዩ ሚኒስትሮችና የተለያዩ የፓርቲውን የፓርላማ ኃላፊዎች እንደሚሰይም በአንቀጹ ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት የኢዜማ መሪ ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በሕገ ደንቡ መሰረት የመንግስትን ሥራዎች የሚከታተሉ የትይዩ ካቢኔ አባላት አዋቅረውና መድበው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ትይዩ ካቢኔ የመንግስትን ስልጣን ያልያዘ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚያቋቁመው የባለሙያዎች ስብስብ ሲሆን ለእያንዳንዱ የመንግስት ካቢኔ ለሆኑ ሚንስትሮች እንደ ጥላ የሆነ ትይዩ ሚንስትር ያለው ማለት ነው፡፡የትይዩ ካቢኔ አባላቱ ከሚከውኗቸው ዋና ዋና ሥራዎች መሀከል ሪቂቅ ሕጎችን መተቸት፣ በፓርላማ ሀሳብ የሚያቀርቡት አባላትን መደገፍና ማሠልጠን፣ የእያንዳንዱን የሚንስትር መሥሪያ ቤቶች ሥራ መከታተል፣ የተፎካካሪ ፓርቲውን የልዩነት ነጥቦች በየወቅቱ ማስገንዘብ፣ መንግሥትን የሚገዳደር የፖሊሲ ንድፍ ማዘጋጀት፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ የተሰየመው የካቢኔ ሚኒስትር ቡድንን በማዋቀርና ኃላፊነቱን በማከፋፈል ፓርቲውን ተፎካካሪ ማድረግ ዋነኛ የሥራ ድርሻዎቹ ይሆናሉ፡፡ ትይዩ ካቢኔ የሚለው እሳቤ ከተዘረዘሩ ተግባሮቹ ባሻገር ከጀርባው ሌሎች ወሳኝ ውጤቶችን ይይዛል፡፡ በስልጣን ላይ ያሉት ሕግ አውጪዎች ተፎካካሪዬ ምን አለ የሚለውን እንዲያውቁ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለመራጩ ደግሞ ለወቅታዊ ተግዳሮቶች ከአንድ በላይ መፍትሔ አለ የሚለውን ማሳየቱ ነው፡፡ ሌላኛው ውጤት ሀሳብ አልባ የሆነ ፉክክርን መቀየሩ ሲሆን ተፎካካሪ የሚባሉ ፓርቲዎችን ወደ አንድ በመሰብሰብ አላማቸውን ላመቀናጀት ዕድል ይሰጣል፡፡ የኢዜማ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ በምንም መልኩ የተጠባባቂ መንግሥትነትና የባለአደራነት ስብስብ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከዚያም ባሻገር አዎንታዊ ሚናውን በመለየት የዴሞክራሲ መሣሪያ፣ የሰላምና የልማት መገልገያ አድርጎ ለውጥ አምጪ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ የሚያሠራና በሕግ አውጪ ወይም በሕግ አስፈጻሚ ውስጥ ቀጥተኛ ሚና ተጫዋች ለማድረግም የሁሉንም ባለድርሻዎች ቅንነትና ዝግጁነት ይሻል፡፡ ረዥም ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል እንዲሉ ዛሬ አሀዱ ተብሎ የሚጀመር እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ግብሩ የሚሰምረው በአዎንታዊነትና ለዴሞክራሲ በሚኖር ቀናዒነት ነው ብለን እናምናለን፡፡ የሀገራችንን የዲሞክራሲ ሂደት በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሊተገበሩ የሚችሉ በጎ ልምምዶችን አጠናክረን በመቀጠል ለትውልድ የሚተላለፍ ከአንድ ምርጫ የዘለለ ፖርቲ እንገነባለን፡፡ ታህሳስ 26፣2014 ኢዜማ ኢትዮጵያ