በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ትኩረት ይሰጥ!


10/28/2021 9:36:21 PM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ትኩረት ይሰጥ! <<የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ሰላም እና ደህንነት መረጋገጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን እንዳለበት ያምናል።>> ወቅቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በበርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተከባ ያለችበት ወቅት ነው። በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተደረገ ያለው ጦርነት ለሀገራችን ብዙ ስጋትን የደቀነ እና አሁንም የሁላችንንም ልዩ ትኩረት የሚሻ እና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑ ይታወቃል። በተመሳሳይ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎች የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፉ፣ ዜጎችን ከመኖሪያቸው እያፈናቀሉ እና እንሰሳትን፣ ሰብልን እንዲሁም ንብረትን እያጠፉ መሆኑን ተገንዘበናል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ሰላም እና ደህንነት መረጋገጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን እንዳለበት ያምናል። አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዜጎች ከማንኛውም ዓይነት አደጋ እና የደህንነት ስጋት ተጠብቀው ሊኖሩ እንደሚገባ ይደነግጋል። እነዚህ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው እና አደጋው ባንዣበበቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ዘላቂ እና የመፍትሔ ሥራዎች እንዲሰራባቸው እንጠይቃለን። በኦሮሚያ ቦረና ዞን፡ በኦሮሚያ ቦረና ዞን በውስጡ ከያዛቸው አስራ ሶስት ወረዳዎች መካከል በአስሩ ማለትም በያቤሎ፣ ዲሎ፣ ኤልውያ፣ ኤልታሬ፣ ኢሬ፣ ዱቡሉቅ፣ ሞያሌ፣ ጉቺ፣ ዳሀስ፣ አረሮ፣ ጎሞሌ እና ሌሎች ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ የድርቅና ምግብ እጥረት አደጋ ስጋት ተጋርጧል። በዞኑ ከወራት በፊት የተከሰተውና አሁንም ድረስ የቀጠለው ድርቅ ከ166,136 በላይ ዜጎችን ለምግብ እጥረት ሲዳርግ በግጦሽ እና መጠጥ ዉሀ እጥረት ምክንያት 200,000 የሚገመቱ የቀንድ ከብቶችን ለጉዳት አጋልጦ 12,000 የሚጠጉ ሞተዋል። በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን ድርቅ እና ምግብ እጥረት ምክንያት በአካባቢው ላይ የሚኖሩ ዜጎች መቋቋም የማይችሉትን ጫና ለመቅረፍ መንግስት ለችግሩ የተሻለ ትኩረት በመስጠት አማራጭ፣ ዘላቂ እና ክትትሎሽ ያለው የፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዳለበት እናሳስባለን፡፡ በደቡብ ኦሞ ዳሳነች ወረዳ: በ2003 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጊቤ ቁጥር 3 የውሃ ሀይል ማመንጫ ግድብ በየዓመቱ የክረምት ወራት የግድቡን ውሃ ማስተንፈስ ሥራ እንደሚከናዉን እና ግድቡን በኃላፊነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅት መሆኑም ይታወቃል፡፡ ላለፉት አስር ዓመታት ከግድቡ በሚለቀቀው ውሃ ምክንያት የሚከሰት ጎርፍ አዲስ ባይሆንም ዘንድሮ ግን ከመስከረም 9/2014 ዓ.ም ጀምሮ 39,092 አባ/እማ ወራዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል። በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ ሳላማጎ፣ ሀመር፣ ኛንጋቶም፣ እና ዳሰነች ወረዳዎች ውስጥ ያሉ 59 ቀበሌያትን በተለያየ መጠን የጎዳ ሲሆን በዳሰነች ወረዳ በሚገኙ 32 ቀበሌዎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በአሁኑ ወቅት ከዳሰነች ወረዳ ኦሞራቴ ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ከግድቡ በተለቀቀ ውሃ ምክንያት የኦሞ ወንዝ በመሙላት መስመሩን ጥሶ በመፍሰሱ ዜጎች ላይ ስጋት ደቅኗል። በአካባቢው የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ለግጦሽ መሬትነት የሚጠቀሟቸው ዲባ: ኘኮን: ሲብል: አባሎኳ እና ሎቤም የተባሉ ለም የግጦሽ መሬቶች በውሃ መጥለቅለቁ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። መንግሥት እንዲህ ያሉ ለሕዝብ ጥቅም የሚውሉ ሃብቶች ዜጎች ላይ የሚያደርሷቸውን የጎንዮሽ ጉዳቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የአደጋ ስጋት እንዳይሆኑ ማድረግን በኃላፊነት ሊሰራባቸው እንደሚገባ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ ሲቀጥልም በአካባቢው ከተከሰተው የውሃ መጥለቅለቅ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ከወዲሁ መንግሥት አተኩሮት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። በተለይም እንዲህ ያሉ አደጋዎቸ ከመድረሳቸው በፊት ቀድሞ በመረዳት ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት የዜጎችን መተዳደርያ እና ንብረት መታደግን እንዲሁም በነዚህ ወረዳዎች አደጋ የደረሰባቸው ዜጎችን ወደቀደመ ሕይወታቸው መመለስን ግንባር ቀደም ስራ ሊያደርገው እንደሚገባ እናሳስባለን፡፡ በአማሮ ልዩ ወረዳ: ራሱን ኦነግ ሸኔ በማለት የሚጠራው እና ከዚህ ቀደም በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው ቡድን በኢትዮጵያ በስተ ደቡብ አቅጣጫ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ጨምሮ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት እያወከ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል። የዚህ ችግር አንዱ ተጋላጭ የሆነዉ አማሮ ልዩ ወረዳ ውስጥ ባሉት ጃሎ፣ ዶሮባዴ፣ ጻልቄ፣ ኮርዴና ሌሎች በጠቅላላው 20 ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ከ50,000 በላይ ዜጎች በአካባቢው የሚገኘው የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በመወረሩ ቤታቸውንና ንብረታቸውን ጥለው በአጎራባች ቀበሌያት ተሰደዋል፤ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የደህንነት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። በተጨማሪም በአጎራባች ያሉት በሲዳማ፣ በአማሮ ኮሬ፣ በቡርጂ፣ በጋሞ እና በጉጂ የሚኖሩ ዜጎች ተመሳሳይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥበቃ ለማግኘት በተደጋጋሚ በአካባቢው ማኅበረሰብ ለመንግሥት ጥያቄ የቀረበበት እና በመንግሥት መፍትሔ ባልተበጀለት አካባቢ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ 300 ሰዎች ህይወት አልፏል። የልዩ ወረዳው መንግስታዊ መዋቅር መንግስታዊ ሥራም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ አገልግሎት የሚሰጠው የአማሮ ኮሬ-ሀዋሳ 213 ኪ.ሜ መንገድም አገልግሎቱ በመቋረጡ ዜጎች በሌላ አቅጣጫ 530 ኪ.ሜ አቋርጠው ከአማሮ ወደ ሀዋሳ እንዲሳፈሩ ተገደዋል። የልዩ ወረዳው ማህበረሰብ 2009 እና 2010 ዓ.ም ላይ ለጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት ያቀረበው አቤቱታ እስከ አሁን ድረስ ዘላቂ መፍትሔ አላገኘም። በሌሎች አካባቢዎችም ጨምሮ ንፁሃን ዜጎችን ማንነታቸውን መሰረት በማድረግ ጥቃት እያደረሰ ያለውን የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ በመዉሰድ በአፋጣኝ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን እንዳለበት እናምናለን። በደራሼ ልዩ ወረዳ እና ኮንሶ ዞን ሠገን ዙሪያ ወረዳ፣ ባስኬቶ ልዩ ወረዳ የዜጎች የራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ የምንደግፈው እና የምንታገልለት መብት መሆኑን በተደጋጋሚ ስንገልፅ መቆየታችን ይታወቃል። የዜጎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ዜጎች ተወያይተው እና እንደሀገርም በአፅንዖት ታይቶ መመለስ ያለበት መሆኑን እናምናለን። በሀገራችን እየተፈጠሩ ያሉት በተለይ ከራስን በራስ ማስተዳደር እና ከመዋቅር ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የፈጠራቸው ነገር ግን በኋላም የሕዝብን ትክክለኛ ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ ናቸው ብለን አናምንም። በደራሼ ልዩ ወረዳ በጋቶ ቀበሌ መንደር 1 እና 2 ላይ ጥር 19-20 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ህዳር 06 ቀን 2013 ዓ.ም እና ጥር 05-06 ቀን 2013 ዓ.ም በዚሁ የመዋቅር እና «ራስን በራስ ማስተዳደር» ጋር ተያይዞ በተከሰተ ግጭት እስከ አሁን የ34 ሰዎች ሕይወትን ሲቀጠፍ ግምቱ በውል የማይታወቅ የንብረት ውድመት አስከትሏል። የአካባቢው ነዎሪዎች በተደጋጋሚ ለመንግሥት ይህንን ግጭት በአስቸኳይ ፈትቶ ወደሰላማዊ ሕይወት እንዲመልሳቸው አቤቱታዎች ቢያቀርቡም እስካሁን መፍትሄ አልተገኘለትም። እንዲሁም በመጋቢት 2003 ዓ.ም የተዋቀረው የሠገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ በማስተናገዱ ጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም እንደ አዲስ በኮንሶ ዞን ተዋቅሯል። ዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ሦስት ወረዳዎች፣ አንድ ከተማ አስተዳደርና አንድ ክላስተር የሠገን ዙሪያ ወረዳ የማያቋርጥ የፀጥታ ስጋት መገኛ ነው። የቀድሞው የሠገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን መቀመጫ የሆነው የሠገን/ጉማይዴ ከተማ በተደጋጋሚ ለነዋሪዎች የደህንነት ስጋትን ያስተናግዳል። በተለያየ ጊዜ በተፈጠረ ሁከት እስከአሁን ከ30 ያላነሱ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተጨማሪም በባስኬቶ ልዩ ወረዳ እና በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ መካከል የሚገኙት የ11ዱ ቀበሌዎች ላይ የሚነሳው የይገባኛል ጥያቄ ከዚህ ቀደም 40,000 የሚደርሱ ዜጎች ከቀያቸው አፈናቅሏል። ዛሬም ድረስ ለነዋሪዎቹ ከፍተኛ ስጋት ከነሆኑም ባሻገር ተፈናቃዮቹን ወደቀደመው ኑሯቸው መመለስ አልተቻለም። የመዋቅር እና የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች በጊዜው መፍትሔ ባለማግኘታቸው ጎን ለጎን በደቡብ ኦሞ ሣላማጎ ወረዳ በሚገኙ አርብቶ አደሮችና በልዩ ወረዳው የአንግላ እና ቡንባሳ ቀበሌዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መካከል በሚነሳው ግጭት የዜጎች ሕይወት እየጠፋ ይገኛል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተሻሽሎ ዘውግን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እና አደረጃጀት እስካልቀየረ ድረስ መሰል ግጭቶች ማስቀረት በእጅጉ አስቸጋሪ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። አሁን በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት ማሻሻያ እስኪደረግበት ወይንም ለዜጎች ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ሥርዓት በሀገራችን እስኪተገበር ድረስ ዜጎችን የመጠበቅ እና አካባቢዎችን የማረጋጋት ስራ በመንግሥት፣ በባለድርሻ አካላት እና. በማኅበረሰቡ ርብርብ ሊሰራ የሚገባ መሆኑን በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን። በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ትኩረት ይሰጥ! ከላይ በተዘረዘሩት አካባቢዎቸ ዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉት ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋዎች የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ፣ ከኖሩባቸው አካባቢዎቻቸው እያፈናቀሏቸው እና ሃብት እና ንብረታቸውን እያወደሙባቸው ይገኛሉ፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ትኩረቶች በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦረነት ላይ በመሆናቸው እነዚህ አካባቢዎቸ ያሉ ዜጎች ሕይወትም ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል፡፡ ኢዜማ መንግሥት በየአካባቢው ያሉ ችግሮችን በአግባቡ በመቃኘት እና ልዩ ትኩረት የሚሹትን አካባቢዎች በአፋጣኝ ለይቶ ዜጎችን ወደመደበኛ ሕይወታቸው የሚመልስ እና እነዚህ አደጋዎቸ ተጨማሪ ስጋት እንዳይፈጥሩ እንዲሁም ለዘለቄታው ዜጎች ሕይወት እንዲሻሻል የሚያደርጉ ፖሊሲ፣ የአሠራር እና የአደረጃጀት ለውጦችን ተግባራዊ እንዲያደርግ እና በተለይም ራስን በራስ ከማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ እየተነሱ ያሉትን ግጭቶቸ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተድርጎ በአግባቡ እስኪፈቱ ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራ እንዲሠራ እና በዘላቂነት እንዲመልስ እንዲሁም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ከፌዴራል የአደጋ ስጋት አመራር ሥራ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት እልባት እንዲሰጥ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡