ሃይማኖትንና ሃይማኖታዊ በዓላትን መንግሥት የግጭት መነሻ ከማድረግ ይቆጠብ!


1/21/2022 7:59:58 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

ሃይማኖትንና ሃይማኖታዊ በዓላትን መንግሥት የግጭት መነሻ ከማድረግ ይቆጠብ! ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ጭምር የምትታወቅበት በአብሮነት የመኖር፣ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ እና የመቻቻል ውብ የሆነው እሴታችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ ጭምር ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የወደቀ ሲሆን በዚሁ ከቀጠልን ደግፈው የያዙት ጠጠሮች ተበትነው እንደማኅበረሰብ አንድ አድርገው ያቆዩንን መልካም ወዳጅነት እንዳናጣ እንሰጋለን፡፡ የቀድሞው አገዛዝ በሕዝብ መራር ትግል እንዲያከትም ከተደረገ በኋላ በትረ ሥልጣኑን የያዙት አመራሮች ሀገራችንን ወደተሻለ ሰላም እና እድገት ያደርሷታል ተብሎ ቢጠበቅም እየተደረገ ያለው ግን ከሚጠበቀው በተቃራኒ እየሆነ በየቀኑ የምንሰማው በሙሉ አሳዛኝና አሸማቃቂ ከሆነ ከርሟል፡፡ ከጊዜ ጊዜ ይታረማሉ ተብለው የታሰቡ ጉዳዮችም ይልቅ ስር እየሰደዱ ለማኀበረሰባችን አብሮ መኖር እንቅፋት እየሆኑ የመጡ ሲሆን በፀጥታ እና የመንግስት መዋቅሮች የሚፈፀሙ ተግባራት ደግሞ ችግሩን የበለጠ እያወሳሰቡት ይገኛሉ፡፡ በትላንትናው ዕለት ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም የቃና ዘገሊላ በዓል ሲከበር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ በተለይም የወይብላ ቅድስት ማርያም እና ታቦተ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ቤተክርስቲያን በመመለስ ላይ ሳሉ የጸጥታ አካላት በፈጸሙት አላግባብ የሆነ ድርጊት ብዙ ሰዎች በመረጋገጥ፣ በድብደባ ጉዳት ሲደርስባቸው ቁጥራቸው በውል ያልተረጋገጠ የበዓሉ ታዳሚዎች ውድ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ የኦሮሚያ የፀጥታ ዘርፍ አካላት ታቦታቱ እየተመለሱ ባለበት ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ማለፊያውን መንገድ አጥረው በመያዝ ታቦታቱን ያጀቡ ምዕመናን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያለባቸውን ማንኛውንም ቁሶች (ግንባር ላይ የሚታሰር፣ እጅ ላይ የሚደረግ፣ የሴቶች የሀገር ባህል ቀሚስ ጥለት፣ ቲሸርት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሆኑ ከበሮዎችን) ይዘው እንዳይገቡ በመከልከላቸው ከፍተኛ የሆነ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ግጭት ሃይማኖታዊ በዓሉ በጸጥታ አካሎች ምክንያትነት ከመረበሹም በላይ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሊደርስ ችሏል፡፡ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት ያጠፉ አካላት ድርጊታቸው በአግባቡ ተጣርቶ እርምጃ ሳይወሰድባቸው በመቅረቱ ተመሳሳይ ጥፋቶች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል፡፡ የፀጥታ ሀይሎች የሕዝብን ደሕንነት ከማስጠበቅ ይልቅ እራሳቸው ስጋት ከመሆን መታረም አለባቸው፡፡ ሀገራችንን ወደ ሃይማኖት ግጭት ለማስገባት ቀን ከሌት የሚጥሩ ኃይሎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ጭምር ተሰግስገው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አካላትን የሚቆጣጠር አቅም እና ፍላጎት ያለው ተጠያቂ የሆነ አመራር ባለመኖሩ ልንወጣው ወደማንችለው ችግሮች ውስጥ እየገባን እንገኛለን፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን የመሸከም ጫንቃ የሌላት በመሆኗ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ለጠፋውም ጥፋት ይቅርታ ሊጠይቅ እንዲሁም ከቤተክርስቲያኗ ሀላፊዎች ጋርም በመምከር ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ሊሰራ ይገባል፡፡ ይህም ጉዳይ እንደ ከዚህ ቀደም ኩነቶች እናጣራለን ተብሎ ብቻ የሚተው እንዳይሆን በፅኑ እናሳስባለን፡፡ ኢዜማ ይህን መሰል ችግር ድጋሚ እንዳይፈጠር በጋራ መሠራት እንዳለበት የሚያምን ሲሆን በዚህ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ያሳውቃል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተፈጠረውን ችግር በጽኑ ያወግዛል፡፡ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፡፡ የ #ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) ጥር 14 ቀን፣ 2014 ዓ.ም