ዋና ገጽ
አወቃቀራችን
ከፍተኛ አመራሮች
ኢዜማን ለምን ይመርጣሉ?
ዐቢይ መልዕክቶች
ስራ አስፈጻሚ
ዕጩዎች
በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይና በስፍራው በተሰማሩ የፀጥታ አባላት ላይ ስለተፈፀመው ግድያ ፍትህ እንጠይቃለን!
2/5/2022 9:15:14 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ
በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይና በስፍራው በተሰማሩ የፀጥታ አባላት ላይ ስለተፈፀመው ግድያ ፍትህ እንጠይቃለን! የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይና በስፍራው በተሰማሩ የፖሊስ አባላት ላይ ስለተፈፀመው የጅምላ ግድያ ያቀረበው ሪፖርት ከፍተኛ ሀዘን እና ድንጋጤን ፈጥሮብናል፡፡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) በተጎጂዎችና በተጎጂ ቤተሰቦች፤ በአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሁም እንዲህ ያለ አስነዋሪ ድርጊት በአገራቸው ቦታ እንዳይኖረው በሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ስም ኮሚሽኑን ማመስገን ይፈልጋል፡፡ ሕዝብና አገር የሚጠቀሙት የገዢዎችን ፊት እያዩ ሳይሆን በመረጃ ላይ በተመሰረተ እውነት በሀቀኝነት በሚሰሩ ተቋማት በመሆኑ የሚዲያ፣ የፀጥታና የፍትህ ተቋማት የኢሰመኮን አርዓያነት እንዲከተሉ እንጠይቃለን፡፡ በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይ የተፈፀመው ያለ ፍርድ ግድያ (Execution without trial) ኢዜማ በአገራችን እንዲሰፍን የሚታገልለት የሕግ የበላይነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መወድቁን ያሳያል፡፡ ዜጎች በእዚህ መልኩ ክቡር የሆነ ሕይወታቸውን እንዲያጡ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊቀርብ አይችልም፡፡ ግድያውን ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት በጋራ እንዲያወግዙት እየጠየቅን መንግስት ከጅምላ ግድያው ጋር በተያያዘ እጃቸው ያለበትን የፀጥታ እና የአስተዳደር አካላት ሁሉ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን፡፡ የዜጎች ደኅንነትን መጠበቅ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ ሲሆን በአካባቢው የፀጥታ አካላት ላይ ጥቃት የፈፀመውንም “ታጣቂ ቡድን” ተከታትሎ ለፀጥታ ሀይሉም ሆነ ለማኅበረሰቡ ስጋት እንዳይሆን በስልት መስራት ግዴታው እንደሆነ መንግስትን ልናስታውስ እንወዳለን፡፡ በግብር ከፋዩ ሕዝብ ሀብት የሚተዳደሩ የመንግስት የመገናኛ ተቋማት ግድያው በተፈፀመበት ወቅት አውቀውም ይሁን በስህተት በጉዳዩ ላይ ለሕዝብ የሰጡት በሀሰት የተቀናበረ መረጃ የተቋማቱን አደገኛ አካሄድ ዛሬም በግልፅ አሳይቷል፡፡ ሰፊ ተደራሽነት ያላቸውና የሕዝብ ሀብት የሆኑ የመንግስት ሚዲያዎች በጓዳቸው ካለ የትላንት ታሪካቸው ተምረው ለተቋቋሙበት ዓላማ፣ ለሕግና ለእውነት ብቻ እንዲሰሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ይህን እኩይ ተግባር በተሳሰተ መንገድ የዘገቡ ሚዲያዎች ሁሉ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀው የኮሚሽኑን ሪፖርት አልያም በራሳቸው መንገድ የተፈጠረውን ትክክለኛ ኩነት በድጋሜ ለሕዝብ እንዲያደርሱ እንጠይቃለን፡፡ ፍትህን በፅኑ እንጠይቃለን፡፡ #ኢዜማ #ኢትዮጵያ