የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን ዛሬ፣ አሁኑኑ ማረጋገጥ ካልቻልን ነገን ማለም አንችልም!


3/7/2022 9:30:07 PM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን ዛሬ፣ አሁኑኑ ማረጋገጥ ካልቻልን ነገን ማለም አንችልም! ውድ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች እንኳን ለየካቲት 29 (ማርች 8) ሴቶች በማኅበራዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለአለም ያበረከቱት አስተዋዕፆ የሚከበርበት አለም አቀፍ የሴቶች ቀን አደረሳችሁ። በአለም፣ በአፍሪካ እና በሃገር አቀፍ ደረጃ ሴቶች ማበርከት የምንችለው አስተዋዕፆ እንዲሁም ያለን ግማሽ በመቶ ያህል ቁጥር የሚመጥን ተጠቃሚነት ከወንዶች እኩል እድሎች ባለመመቻቸታቸው ብቻ እውን ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሃገራችን በገባችበት ቀውስ እና በሚፈጠሩ ግጭቶች ዋነኛ ተጎጂ ሴቶች የመሆናቸው ሚስጥርም ሴቶችን ከጥቃት የሚከላከል እና ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ የሚያበቃ ስርዓት ባለመገንባታችን ነው። እንኳን በጦርነት እና በቀውስ ይቅርና አንፃራዊ ሰላም ባለበት ጊዜ እና ቦታም ሴቶች በቤታቸውና በአካባቢያቸው ሰላም የላቸውም። ሴቶች ዛሬም ከቤት ውስጥ ጥቃት እስከ በአካላቸው ላይ የመወሰን መብትን መነጠቅ፤ መደፈር፤ መጠለፍ፤ ህፃናት እና ታዳጊ ሴቶች ያለእድሜ እና ያለፍላጎታቸው መዳር፤ በፖለቲካው ዘርፍ ወሳኝነትን አለማግኘት፤ ለሚሰሩት ስራ ከወንዶች እኩል ክፍያዎች አለመከፈል፤ ከትምህርት ገበታ መራቅ፤ ስራ የሌላቸው ወጣት ሴቶችም ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ፤ በአጋሮቻቸው መጠቃት እና ሌላም ብዙ ችግሮቻቸው ተጠናክረው ቀጥለዋል! ይህንን ጠንክሮ የሚከላከል እና እኩልነት የሚያረጋግጥ የህግ፣ የፖሊሲ፣ የትግበራ እና ማኅበራዊ ስርዓት የለንም። የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን "የፆታ እኩልነት ዛሬ ለዘላቂ ነገ" በሚል መሪ ቃል ይከበራል። በአካባቢ ጥበቃ እና ክብካቤ ጉዳይ ምላሽ በመስጠት ላይ ሴቶች የሚጫወቱትን ሚና በማጉላት ላይ ያተኩራል። ከ80 በመቶ በላይ ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ ለተመሰረተ ሃገር የአካባቢ ጥበቃ እና ክብካቤ ጉዳይን እንደትልቅ አጀንዳ መውሰድ ዘላቂ ልማትን እና ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በተለይም በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ኑሯቸው በበለጠ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ ስለሚያደርጋቸው የአካባቢ ጥበቃ እና ክብካቤ ጉዳይ ላይ የፖሊሲ ለውጦችን ካላደረግን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት ላይ ተጨባጭ ስራ ካልሰራን ስለሃገራችን "ብልፅግና" ማውራት ቀቢፀ-ተስፋ ነው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) ማኅበራዊ ፍትህ መርኋ የሆነ፣ ዜጎች ሁሉ በእኩልነት የሚኖሩባት እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ያደረገች ኢትዮጵያን ማየት ከፈለግን ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ በተለያየ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ወደፊት ማምጣት እንዲሁም በሁሉም የማኅበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እና በራሳቸው ጉዳይ ላይ ወሳኝ እንዲሆኑ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሀገር ህልማችንን ለማሳካት አንድ እርምጃ ወደፊት ይወስደናል ብሎ በፅኑ ያምናል። የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን ዛሬ፣ አሁኑኑ ማረጋገጥ ካልቻልን ነገን ማለም አንችልም! ኢትዮጵያችን ለሁላችንም እኩል እድሎችን የምትሰጥ እንድትሆን ስራችንን ዛሬውኑ፣ አሁኑኑ እንጀምር! መልካም የሴቶች ቀን ለሁላችንም ሴቶች! ፅዮን እንግዳዬ የኢዜማ ወጣቶች ጉዳይ ተጠሪ #ሴቶች_ለማኅበራዊ_ፍትህ #ኢዜማ #ኢትዮጵያ