የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበት አሰቃቂ ግድያ በጥብቅ ይኮንናል።


3/14/2022 9:36:11 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበት አሰቃቂ ግድያ በጥብቅ ይኮንናል። ከዳኝነት ውጪ የሚፈፀሙ እንደዚህ ያሉ ግድያዎች ዜጎች በሕጋዊ ሥርዓት ላይ ፈፅሞ እምነት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ፣ የደቦ ፍርድን የሚያበረታታና በአገራችን ሥርዓት አልበኝነት እንዲንሰራፋ የሚያደርግ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን መሰል አስነዋሪ ድርጊቶች ሲፈፀሙ እናስተውላለን። ተገቢ የማጣራት እርምጃ ተወስዶ ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት ለሕግ ይቀርባሉ የሚሉ ተደጋጋሚ መግለጫዎች ከመንግሥት ቢሰጡም፣ ሕግ ፊት ቀርቦ የተጠየቀ አካል እስካሁን ማየት አልቻልንም። ይህም ሁኔታ በአገራችን የደቦ ፍርድ እንዲያብብ፤ ሥርዓት አልበኝነትም እንዲነግስ በር ከፍቷል። እንደዚህ ያሉ ሕገ-ወጥ ተግባራት ሳይውሉ ሳያድሩ ካልተስተካከሉና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ካልተደረገ በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው አደጋ ውስጥ እንወድቃለን። ስለሆነም መንግሥት በዚህ አስነዋሪና አፀያፊ ድርጊት ላይ የተሰማሩ የፀጥታ ኃይሎችን ማንነት በማጣራት ለሕዝብ ግልፅ እንዲያደርግና ሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች ካሉም የፀጥታ መዋቅሩን በመፈተሽ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርባቸው እናሳስባለን። የሟች ቤተሰቦችም ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙ እንጠይቃለን። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን እያደረገ ስላለው ጥፋቶችን የማጋለጥ ስራ ትልቅ ክብር እና አድናቆት እንዳለን በዚህ አጋጣሚ ልናሳውቅ እንወዳለን፡፡ ለሌሎች ተቋማትም ትልቅ ተምሳሌትነት ነው፡፡ #ኢዜማ #ኢትዮጵያ