ከኢትዮጵ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ዙሪያ የተሰጠ መግለጫ


5/10/2022 6:55:13 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

ከኢትዮጵ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ዙሪያ የተሰጠ መግለጫ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዘመናት በየጊዜው በተለያዩ ኹነቶች እና ተሳታፊ አካላት በሚደረት እና በሚወሳሰብ የችግር አረንቋ ውስጥ ለተዘፈቀው መሀከልየኢትዮጵያ ፖለቲካ በጊዜ ሂደት ብቸኛው የመውጫ አማራጭ መንገድ ሕዝብ ከታችኛው ከወረዳ ጀምሮ ራሱ ባለቤት ሆኖ በሚፈጥረው አደረጃጀት ላይ ተመስርቶ በየደረጃው የሚመሩትን አመራሮቹን ከወረዳ በመወከል ወይም መምረጥ የሚችልበት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በመፍጠር ብቻ መሆን እንዳለበት የፀና እምነት ይዞ ዜግነት ላይ የተመሠረተ ፓርቲ ነው፡፡ ከምስረታው በኋላም ሀገራችን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ሰላሟ የተጠበቀ፤ ማኅበራዊ ፍትህ የሰፈነባት፤ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት እና የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚጠበቅባት ሀገር እንድትሆን በመሻት ፅኑ እምነት ይዞ በሰላማዊ ትግል ሥልጣን ከሕዝብ ድምፅ እንደሚመነጭ በማመን ለተግባራዊነቱም ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ኢዜማ ግንቦት 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከተ የሚገኝ እና በየወቅቱ የሚገጥሙትን ወጀቦች በጥበብና በበሳል አመራር እያለፈ በመጓዝ ላይ ያለ ፓርቲ ነው። ፓርቲያችን የተቋቋመበትን ራዕይ ለማሳካት በቀጣይ ከሚፈጽማቸው ተግባራት መሀከል አንዱ እና ዋነኛው የሆነው አንደኛ መደበኛ ጉባኤ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር በፓርቲው ደንብ አንቀፅ ቁጥር 6.2.24 መሠረት ፓርቲያችን በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ መደበኛ ጉባኤውን ማከናወን እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡ በዚህም ድንጋጌ መሠረት በመጪው ሰኔ 11 እና 12 ቀን 2014 ዓ.ም አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን በሚያደርግበት ጊዜ ፤ በፓርቲው ደንብ አንቀጽ ቁጥር 4.2 መሠረት የፓርቲው 4 አካላት እና የውጪ ኦዲተር የሚያቀርቡትን ሪፖርት አዳምጦ ውይይት በማድረግ እና በፓርቲው ደንብ መሠረት በጉባኤው የሚመረጡ ከፍተኛ አመራሮችን ምርጫ የሚያከናወን ይሆናል፡፡ በፓርቲው ህገ ደንብ አንቀጽ ቁጥር 21 መሠረት የፓርቲውን መደበኛ ጉባኤ ለማከናወን የሚያስችሉ አካላትን እንዲያቋቁም እና የአሠራር ሥርዓትና መስፈርት እንዲያዘጋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የምርጫ ሂደቱን የሚመራ ሦስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ እንዲሁም ጉባኤውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ የዝግጅት ተግባራትን የሚያስተባብር ሰባት አባላትን ያቀፈ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ከመጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በማቋቋም ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ የፓርቲውን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች በተጨማሪ የፓርቲው ህገ ደንብና ዲስፕሊን ኮሚቴ፤ የምርጫ ክልሎች፤ ሌሎችም የፓርቲው አካላት፤ ምርጫ ቦርድ እና በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ህግና ደንብን በተከተለ እና ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እየሠሩ ይገኛል፡፡ በፓርቲው ህገ ደንብ መሠረት ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያቋቋማቸው ሁለቱ ኮሚቴዎች አስካሁን የሚከተሉትን አንኳር ተግባራት እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እነርሱም፡- • ኮሚቴዎቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ፤ ኃላፊነትና ተግባር እንዲሁም ሥራቸውን የሚከውኑበትን መመሪያ ማዘጋጀትና ማጸደቅ፤ • የኮሚቴዎቹን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል የሥራ እቅድና በጀት ማዘጋጀትና በሚመለከተው አካል ማጸደቅ፤ • ኮሚቴዎቹን በንዑስ ኮሚቴዎች ማዋቀር፤ በመዋቅሩ መሠረት የሥራ ክፍፍል ማድረግ እና ለሥራው የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ማሰባሰብ፤ • በጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ አባላትን የመላክ በህገ ደንብ መብት የተሰጣቸው የምርጫ ክልሎች የሚልኩትን የተሳታፊ ብዛት እና ስብጥር ምን መምሰል እንደሚኖርበት በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማጸደቅ እና ውሳኔውን ለምርጫ ክልሎች መላክ፤ • የዕጩ ተወዳዳሪዎች መስፈርት እና የጊዜ ሰሌዳ በሚመለከታቸው አካላት ተዘጋጅተው እንዲጽቁ እና ለምርጫ ክልሎች እንዲደርስ ማድረግ፤ • ከምርጫ ቦርድ በህገ ደንቡ ላይ እንዲሻሻሉ ጥቆማ የተሰጠባቸው ነጥቦችን መሠረት በማድረግ የህገ ደንብ ማሻሻሉን ሥራ የሚያከናውኑ ንዑሳን ኮሚቴዎች ውስጥ በጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ ማቋቋም፤ • እንዲሁም የጉባኤ ማከናወኛ ስፍራን የመለየት ሥራ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይህ ጉባኤ በተገቢው ሁኔታ እንዲከናወን በቀጣይ እስከ ጉባኤው መዳረሻ ቀናት እና ጉባኤው በሚካሄዱባቸው ቀናት ውስጥ የተቋቋሙት ኮሚቴዎችም ሆነ ሌላ በህገ ደንቡ መሠረት ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ቀጣዮቹን አንኳር ተግባራት የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ • የምርጫ ቅስቀሳ ማከናወኛ የሥነ - ሥርዓት መመሪያ ማዘጋጀትና ማፀደቅ፤ • የምርጫ ማከናወኛ ሥርዓት ማዘጋጀትና ማጸደቅ፤ • የጉባኤ ተሳታፊዎችን ማንነት እና አድራሻ ከየምርጫ ክልሉ፤ እንዲኹም ያለድምጽና በድምፅ በህገ ደንብ አንቀጽ ቁጥር 4.1.3 መሠረት የመሳተፍ መብት ከተሰጣቸው የፓርቲው አካላት ማሰባሰብ፤ • ጉባኤውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ግብዓቶችን ማሟላት፤ • በመጨረሻም በሰኔ 11 እና 12 ቀን 2014 ዓ.ም ጉባኤውን እጅግ በተሳካና በደመቀ ሁኔታ ማካሄድ፤ እነዚህን ተግባራት ግልጽ፣ ተዓማኒ እና እውነተኛ በሆነ መንገድ ማከናወን ለፓርቲያችን ውስጠ ዴሞክራሲ ግንባታ፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል መለወጥ አዋንታዊ አስተዋፅዖ ማድረግና አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ በመውጣት ለሕዝባችን ተስፋ መስጠት በሚያስችል መልኩ የፓርቲውን አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ማከናወን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አምነን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በቀጣይም የፓርቲውን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ሂደት የሚያሳዩ መረጃዎችን በየደረጃው በተለያዩ ጊዜያት የማስተዋወቅ ሥራ ለሕዝባችን ፤ አባላትና ደጋፊዎቻችን የምናስተዋውቅ መሆኑን ከወዲሁ እየገለጽን የሚመለከታቸው አካላትም በሂደቱ ውስጥ ጠቃሚ የሆነ በጎ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ