የዜጎች መድረክ


2/19/2021 2:54:39 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

የዜጎች መድረክ 076 በግርማ ሞገስ ላይ የተፈፀመው ግድያ ፖለቲካዊ ነው ቢሾፍቱ ከተማ የአድአ ምርጫ ወረዳ 1 ሊቀመንበር የነበሩት እና እሁድ የካቲት 07 ቀን 2013 ዓ.ም በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ያለፉት ግርማ ሞገስ፣ ግድያ ፖለቲካዊ ነው ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ፡፡ ኢዜማ፣ ረቡዕ የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም በዋና ፅህፈት ቤቱ በመስፍን ወልደማሪያም አዳራሽ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ይህን ያለው፡፡ የቢሾፍቱ ፖሊስ ግርማ ሞገስ፣ አባል ስለመሆኑ እያጣራው ነው ሲል ለመገናኛ ብዙሃን የሰጠውን መግለጫ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡ ፓርቲው የካቲት 03 ቀን 2013 ዓ.ም ለቢሾፍቱ ፖሊስ በፃፈው ደብዳቤ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ሌላ የኢዜማ አባል የሆነን ሰው መኖሪያ ቤት በፈተሸበት ወቅት የወሰዳቸውን የኢዜማን መገልገያ ሰነዶች እንዲመልስ በጠየቀበት ደብዳቤ፣ ግርማ ሞገስን ወክሎ መላኩን ተከትሎ ግርማ ሞገስም ከፖሊስ ጋር ሲነጋገሩ እንደነበር ገልጿል፡፡ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ የካቲት 03 ቀን 2013 ዓ.ም ይህንኑ ደብዳቤ ማሕተም እና ፊርማ አስፍሮ መቀበሉን አሳውቋል፡፡ ‹‹የሕግ የበላይነት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገራችን እንዲሰፍን የሚደረገው ትግል የብዙዎች መራር ትግል እና መስዕዋትነትን የጠየቀ እንደሆነ ይታወቃል›› ያለው ኢዜማ አባሉ ግርማ ሞገስን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ስለእኩልነት እና ፍትህ ሲሉ ዋጋ የከፈሉ ኢትዮጵያዊያን መስዕዋትነት ቁጭት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት ለሚያደርገው ትግል ተጨማሪ ብርታት እንደሚሆነው እንጂ በዚህ ምክንያት በፍፁም ወደኋላ እንደማይል አስታውቋል፡፡ ‹‹እየሞትንም ቢሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ከመገንባት የሚያቆመን ምንም ኃይል የለም፡፡ ይህ ለማንም ግልፅ ሊሆን ይገባል።›› በማለት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡ መንግሥት የግርማን ሕይወት የቀጠፉትን ወንጀለኞች አድኖ ሕግ ፊት ባስቸኳይ እንዲያቀርብ በመግለጫው የጠየቀው ኢዜማ፣ ግርማን ጨምሮ በአባሎቹ ላይ ወከባ እና ማስፈራሪያ ሲያደርጉ የነበሩ የቢሾፍቱ የፓርቲና የመንግሥት ኃላፊዎች የምርመራው አካል እንዲሆኑ ሲል ጠይቋል፡፡ ወከባውንም ሆነ ማስፈራሪያውን ቀድሞ እንዲያውቁ የተደረጉት የክልሉም ሆኑ የፓርቲው ከፍተኛ ኃላፊዎችም ግድያውን እንዲያወግዙ ሲል ኢዜማ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ የማጣራት ሥራውን በሚመለከት ማገዝ የምችለውን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ ያለው ኢዜማ፣ የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት ይህን ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ለሰላማዊ እና ፍትሀዊ ምርጫ ከልቡ የተዘጋጀ መሆኑን ማወቅ የምችለው ብሏል፡፡