የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮች እና አባላት «ደሜን ለእናት ሀገሬ» በሚል መሪ ቃል ትላንት ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት በመገኘት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ።


8/30/2021 2:10:07 AM
ፒዲኤፍ ዳውንሎድ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮች እና አባላት «ደሜን ለእናት ሀገሬ» በሚል መሪ ቃል ትላንት ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት በመገኘት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ። በደም ልገሳው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ በጦርነት ላይ እንደምትገኝ አስታውሰው፤ በጦርነቱ ላይ የማይሳተፉ ዜጎች ካሉባቸው አንዱ ኃላፊነት ውስጥ ለሀገር ሲሉ እየተዋደቁ ለሚገኙ የሠራዊቱ አባላት የደም እጥረት እንዳይከሰት ደም መለገስ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ኢዜማ ይህን ዓይነቱ የደም ልገሳ ሲያካሄዱ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ አስረድተው ወደፊትም እንደሚቀጥሉበት ገልፀዋል። ደም ከመስጠት ባሻገርም ለጦርነቱ የሚያስፈልጉ እገዛዎች እንዲኖሩ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የኢዜማ አባላትን በማስተባበር በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል 250,000 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። «ፖለቲካ የሚኖረው አገር ሲኖር ነው!» ያሉት መሪው የሀገርን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነገር ሲከሰት ዜጎች አብረው መቆም እንዳለባቸው በአፅንዖት ተናግረዋል። ፖለቲካ ፓርቲዎች ደም ከመስጠት ባሻገር ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱም ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ግጭቱን በሚመለከት የራሳቸው ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባና ማኅበረሰቡን በዛ ዙሪያ ማስተማር እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሚደረጉ ሁለንተናዊ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።