For International Support Click Here

ይጀምሩ ኢዜማን ይቀላቀሉ
ከኢትዮጵ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት ዙሪያ የተሰጠ መግለጫ
 
5/10/2022 6:55:13 AM
 
ሙሉውን ያንብቡ

ለመሪነት የዕጩ ምልመላ
 
5/10/2022 2:35:44 AM
 
ሙሉውን ያንብቡ

Previous Next 



 

 

Previous Next 

ስለ እኛ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ግንቦት 2 ቀን 2012 ዓም ከ312 የምርጫ ወረዳዎች ተወክለው በመጡ አባላት የተቋቋመ ሲሆን፤ዜግነትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ፍትህ ለማስፈን የሚሠራ፣ በኢትዮጵያ አንድነት ፅኑ መሰረት ላይ የቆመ፣ ያልተማከለ ፌደራላዊ አስተዳደር መርህን የሚከተል የፖለቲካ ፓርቲ ነው። ኢዜማ በኢትዮጵያ ውስጥ ዕውቀትን መሰረት ያደረጉ የፖሊሲ አማራጮችን በመተግበር ሁለንተናዊ ልማት ለማምጣት፣ ማንነት ላይ ላተኮረ ፖለቲካ መንስዔ ለሆኑ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ ዜግነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት፣ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት እና ፍትህ ለማስፈን የሚተጋ ሀገራችንን ካለችበት የድህነት ወለል አንስቶ ወደ ተሻለ የሥልጣኔ እና የዘመናዊነት ከፍታ የማድረስ ህልም ያነገበ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡




መርሆዎቻችን

  • ለእውነተኛና ዘላቂ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነትን ወደ ዜጎች በማቅረብ ፖለቲካዊ ግልጽነትንና ተጠያቂነት ባህል ማጠናከር፣ የመልካም አስተዳደር መሠረት በመሆን፣ ለፈጣን የማኅበራዊ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና መጫወት ለማንነት ፖለቲካ መንስኤ ለሆኑት ችግሮች መፍትሄ የሰጠና፣ ዜግነት ላይ ብቻ ያተኮረ የፖለቲካ አመለካከት ማስረፅ
  • ኢትዮጵያን ሕዝብ ልዩ ማንነትና ባህላዊ እሴቶች መጠበቅና መንከባከብ
  • የማኅበረሰባችን የሞራል መሠረት፣ ማኅበራዊ ፍትህ የማስፈን፣ ለድሆችና ለደካሞች ድጋፍና ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ
  • ለተከታይ ትውልድ ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የተጎናጸፈች፤ የተፈጥሮ ሀብቷንና ውበቷን የተንከባከበች ኢትዮጵያን ማስረከብ


ራዕይ

የኢዜማ ራዕይ፣ ኢትዮጵያ አገራችን የእያንዳንዱ ዜጋዋ ፖለቲካዊ፣ ሰብዓዊና ኢኮኖሚ መብቶች የተከበሩባት፤ ማኅበራዊ ፍትህ የሰፈነባት፤ በዜጎቿ ጽኑ አንድነት ማዕቀፍ፣ የተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች ሳይበላለጡ በነፃነት የሚስተናገዱባትና የውበቷ መገለጫ ብቻ የሆኑባት፤ ሰላምና መረጋጋት የተረጋገጠባት፣ በላቀ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት ላይ የተመሠረተ ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የተጎናጸፈች፤ ሁሉም ዜጎቿ የሚኮሩባት ታላቅና ገናና ሀገር ሆና ማየት ነው።

ተልዕኮ

የኢዜማ ተልዕኮ፣ሰፊ የሕዝብ መሠረት ያለው የመንግስት ሥልጣን ባለቤት በመሆን እና የፓርቲውን መርሆች መሠረት ያደረጉ፣ የእድገት፣ የብልጽግና የሥልጣኔ ፖሊሲዎችን በመቅረጽና በማስፈጸም፣ በራዕዩ ላይ የተቀመጠችውን ዘመናዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው።

የኢዜማ አመሰራረት

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሀገራችን የፖለቲካ ፖርቲዎች ታሪክ ለመጀመረያ ጊዜ ከተለመደው የፖርቲዎች ውህደት፣ ግንባር መፍጠር፣ ጥምረት እና መሰል አካሄዶች የነበረባቸውን ክፍተት በማጥናት ፓርቲዎች እራሳቸውን አክስመው እና ሁሉም አባሎቻቸው ወደየምርጫ ወረዳቸው በመሄድ እንደ ግለሰብ አባል በመሆን የተመሰረተ ፓርቲ ነው።

የፖለቲካ ፍልስፍና

የኢዜማ የፖለቲካ ፍልስፍና መሰረት ማኅበራዊ ፍትህ (social justice) ነው። እንደኛ ሀገር ዓይነት በዜጎች መሀከል መጠናቸው እና ቁጥራቸው የበዛ ልዮነቶች ያሉበት፣ ድሆች እና ደካሞች ልዩ ጥበቃ የሚሹበት ሀገር ላይ ማኅበራዊ ፍትህ እዲሰፍን መስራት ተገቢ ነው ብለን እናምናለን።

ሕገ መንግሥት

ኢዜማ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ያምናል። የሚደረገው የሕገ መንግሥተ ማሻሻያ የሚመለከታውን ኃይሎች (stake holders) ባሳተፈ መልኩ ሊደረግ የሚገባው መሆን አለበት ብለን እናምናለን። ሕገ መንግስት ምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ አልያም በሆነ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጣ ኃይል በራሱ ልክ ሰፍቶ ዜጎችን የሚያለብሳቸው ሰነድ አይደለም የሚል ፅኑ አቋም አለን። ለዚህ አበክረን እንሰራለን።

ፌደራሊዝም

ያልተማከለ የመንግሥት አስተዳደር፣ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትነትን ወደ ዜጎች በማቅረብ፣ የፖለቲካዊ ግልጽነትንና ተጠያቂነት ባህል በማጠናከር፣ የመልካም አስተዳደር መሰረት በመሆን፣ ለፈጣን የማኅበራዊና የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት እናምናለን። የፌደራል ሥርዓታችን ከቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች መመዘኛዎችን በማከል ሊሻሻል እንደሚገባ እናምናለን።

እሴቶች

  • ተጠያቂነት (Accountablity)፤ የኢዜማ አባላት በየደረጃው በምንወስደው ኃላፊነት እና በምናከናውነው ተግባር ሁሉ በሙሉ ተጠያቂነት ሰሜት እንሠራለን፤ የሀገር እና ሕዝብ ጥቅም በማስቀደም የዕለት ተዕለት ተግባራችንን እናከናውናለን፡፡ በዚህ ምክንያት ለሚፈጠሩ ስህተቶች ሌሎች ላይ ከማሳበብ ይልቅ ሙሉ ኃላፊነት ወስደን እናርማለን፤ በሥልጣን ላይ ሆነን ለሚፈጠር ስህተት ከኃላፊነት በፈቃደኝነት እስከመልቀቅ ድረስ ለሚደርስ ውሳኔ ዝግጁ ነን፡፡ የሕዝብ ኃላፊነት (ሥልጣን) አደራ እንጂ ውርስ ነው ብለን አናምንም። ይህንን በተግባር እናሳያለን።
  • ሠላማዊነት (Being peaceful) ፤ የኢዜማ አባላት በምንኖርበት፣ በምንሠራበት አካባቢ ሁሉ ሠላማዊ ሆነን እንንቀሳቀሳለን። ለሠላም ዘብ እንቆማለን። በአጋጣሚ በሚፈጠሩ ግጭቶች ከማባባስ ይልቅ ነገሮችን በጥሞና በመመርመር ለሠላማዊ መፍትሔ በር ከፋች መሆንን እንመርጣለን፤ እንተገብራለን፡፡ የሠላምን ጥቅም በጦርነትና ብጥብጥ ውስጥ ገብተን ሳይሆን ማኅበረሰቡ ቀድሞ እንዲገነዘብ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እናደርጋለን።
  • ትብብር (Cooperation)፤ ለሀገራችን ሠላምና አንድነት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረን የምንሠራ ሲሆን፣ በፓርቲያችን ውስጥ ደግሞ የቡድን ሥራ ባሕል አድርገን እንተገብራለን፡፡ በሀገር ጉዳይ ከማንኛውም የፖለቲካ ኃይል ጋር በትብብር የምንሠራ ሲሆን፤ ሁሌም ፉክክራችን በፖሊሲ አማራጭ እንጂ በሀገር ሕልውና ላይ አድርገን አይሆንም፡፡ ሀገርን መያዣ አድርጎ የሚደረግ ፉክክር አውዳሚና አጥፊ በመሆኑ ይህን ሰሜት ወደ ትብብር እንዲመጣ አበክረን እንሠራለን፡፡
  • ውይይት (Dialouge)፤ በሀገራችን ያሉ ማንኛውም ዓይነት ጉድለቶች ለውይይት ቀርበው መፍትሔ የሚፈለግላቸው ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ልሂቃን በውይይት ባይስማሙ ይህን ጉዳይ ለግጭት ሳይሆን ለሕዝብ ብያኔ ለማቅረብ መዘጋጀት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ የሕዝብ ውሣኔ የተሣሣተ ቢሆን እንኳን ከመቀበል ውጭ ለመቀልበስ የሚደረግ ጥረት ተገቢ ነው ብለን አንወስድም፡፡ ስህተት የሚታረመው ሕዝቡ ስህተት መሆኑን አምኖ በቀጣይ በድምፅ ሲበይን ብቻ ነው፡፡ ውይይት የችግሮች መፍቻ ቁልፍ መንገድ ሲሆን የሠላምን ትሩፋት ለማጣጣም ጊዜም የሚሰጥ የሥልጡን ዜጋ መገለጫ ነው ብለን እናምናለን፡፡
  • ልኅቀት (Excellence)፤ የኢዜማ አባላት በሁሉም ተግባራችን በጥራት ለመከወን በምናደርገው ጥረት ምሣሌ ሆነን እንድንቀርብ እንጥራለን፡፡ የኢዜማ አባላት በግል ሥራችን ይሁን ተቀጥረን በምንሠራበት ወይም በመንግሥት ተቋማት ሁሉ የተጣለብን ኃላፊነት በብቃት እና በጥራት በመወጣት ምሳሌ የምንሆን ፈጻሚ ለመሆን እንጥራለን።


ኢዜማን ይቀላቀሉ


ጆሞ ኬንያታ መንገድ, አዲስ አበባ

+251 5 258024/25