አወቃቀራችን

ኢዜማ በሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ አዲስ አይነት አደረጃጀትና መዋቅር ይዞ የተቋቋመ ፓርቲ ነው፡፡ ይህም ላቅ ያለ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን የድርጅት ፍላጎትና ጥቅምን ከሃገር ፍላጎትና ጥቅም እንዲለይ የሚያስችል ነው፡፡የኢዜማ አደረጃጀት ሁለት የተለዩ ቅርጾችን ይዞ መጥቷል። የመጀመሪያው በፊት የተለመደውን ፓርቲን በጥቂት ምሁራን ወይም የሚግባቡ ግለሰቦች በመመስረት ለሕዝብ ለማስተዋወቅ (ሕዝባዊ የማድረግ ሙከራ) በመተው ከምሰረታው ጀምሮ ሕዝባዊ አደረጃጀት እንዲይዝ ተደርጎ ከፓርቲው ምስረታ በፊት በ312 የምርጫ ወረዳዎች የተዘረጉ መወቅሮች ወኪሎቻቸውን ልከው የመሰረቱት ፖርቲ ነው። ሁለተኛው ለየት የሚለው በሀገራችን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የኢዜማ አደረጃጀት የፓርቲ መሪ እና ሊቀመንበር መዋቅርን መሰረት አድርጎ መደራጀቱ ነው። ይህ አደረጃጀት የመንግሥት ሥልጣን የሚይዘውን የፓርቲ ክንፍ እና የፓርቲውን የቀን ተቀን ድርጅታዊ ሥራዎች የሚሠራውን መዋቅር ከአሁኑ በመለየት ኢዜማ የመንግሥት ሥልጣንን እና የፓርቲ ሥራን ቀላቅሎ የመሥራት መንገድን በር ዘግቶ የተነሳ ብቸኛ ፓርቲ ያደረገዋል። የፓለቲካ ሥራ ሀገር ከመምራት ጋር የሚገናኝ ሥራ ነው። ሀገርን ለመምራት ደግሞ ሀገር የሚመራበት ሕግ እና ደንቦች እንዲሁም በተለያየ ዘርፍ ላይ ተግባራዊ የሚሆኑ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን መቅረፅ ያስፈልጋል። እነዚህ የተጠቀሱት ሰነዶች ተግባራዊ ሲሆኑ ዘር፣ ሀይማኖት፣ ቋንቋ፣ ፆታ እና ዘርፈ ብዙ ንዑስ ማንነቶችን መሰረት አድርገው ሳይሆን የአንድ ሀገር ዜጋ መሆንን መስረት አድርገው ነው። በዚህ ዋና የፖለቲካ እና የመንግስት አስተዳደር መርህ ምክንያት ኢዜማ ፖለቲካ የዜግነት ሥራ ነው ብሎ ያምናል። የፖለተካ ፓርቲዎች መሰረት ሊያደርግ የሚገባው ዜግነት ነው። የፖለተካ ፓርቲ አባልነትም እንዲሁ። የኢዜማ ብቸኛው የአባልነት መስፈርት ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ ነው።